ሰለ ቤተ-ክርስትያን ዝም አልልም


ዐምደ ሃይማኖት የሚባለው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምስጢር ላይ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ርሱ ራሱ በግ ደሙም ወይን፤ ርሱ ሙሽራ ጐኑም የሕይወት ውሃ ምንጭ፤ ርሱ መምህር የአፉም ትንፋሽ የዕጣን መዐዛ፤ ርሱ መብራት መስቀሉም መቅረዝ፤ ርሱም የገነት ዛፍ የጸጋውም ወንጌል መዐዛው ያማረ አበባ፤ ርሱ የጽድቅ ፀሓይ ሐዋርያቱም የብርሃን ከዋክብት፤ ርሱ የበረከት ማዕድ ካህናቱም የምስጢር አገልጋዮች፤ ርሱ የቅድስና ልብስ ዲያቆናቱም በልብስነቱ ዘርፍ ኾነው ልብሰ ተክህኖውን የሚከብቡት የወርቅ ጸናጽል፤ ርሱ እረኛ ያመኑበትም የምስጢር በጎች፤ ርሱ ንጉሥ ሰማዕታቱም የመንግሥትን አዳራሽ የሚያስጌጧት ዕንቊዎች፤ ርሱ አውነተኛ የወይን ስፍራ መነኮሳቱም ለሚያዩት ሰዎች ለአይን ያማረ የጽድቃቸውም ፍሬ በሚያነብበው ሰው አፍ የሚጣፍጥ የወይን ዘለላዎች ናቸውና፡፡
አንባቢያን ሆይ ይህን የተናገረው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ነው፡፡ ታድያ አሁን በአባቶቻችንና በእናቶቻችን አለፍ ካለም በአያቶቻችን እድሜ (ማለትም 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) የተነሱ ፕሮቲስታንቶች ሆኑ ተሐድሶዎች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ወንገልን አትሰብክም፣ ክርስቶስን ረስታዋለች፣ ክርስቶስን አትሰብክም ቢሉ ማን ያምናቸዋል፡፡
እኔ ግን ስለ ቤተ-ክርስትያኔ ዝም አልልም እናገራለሁ እጽፋለሁ!!! ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚስጢር ባለቤት፤ የሞላች የሰፋች ይህ ቀረሽ የማትባል ስንዱ እመቤት፤ የሥልጣኔ መገኛ የኢትዮጵያ ባለውለታ እንደሆነች ለዘላለም እመሰክራለሁ!!!

ዳግመኛም ድንግል መልአኩን እንዳልኸኝ ይኹንልኝ አለችው ያን ጊዜ ቃል ከርሷ ሥጋን ተዋሐደ (ሉቃ ፩፥፴፰) አይታ እንዳትደነግጥ ተመልክታም እንዳትፈራ ሰው በኾነ ጊዜ ከርሱ ጋር አራቱን እንስሳውን አላመጣም በሰማይ ሥርዐት የተጠበቁ ሰማያውያኑን በዚያ ተወ (ራእ ፬፥፮-) በዚኽም ለቅዱሳን መላእክት የሚረባ ምድራዊት ሥርዐትን ሠራ (ሉቃ ፪፥፲፫) በዚያ በአባቱ ቀኝ አለ በዚኽም በእናቱ ማሕፀን ውስጥ አለ፤ በዚያ ብቻውን የማይታይ ኀይል ነው በዚኽም የማይዳሰስ ኀይል ከሥጋው ጋር የሚዳሰስ ኾነ፤ በዚያ ተሸካሚዎቹ እሳት የተሣለባቸው አራቱ እንስሳ ናቸው (ሕዝ ፩፥፬-፳፮) በዚኽም ተሸካሚዎቹ ለሰውነት መንገድ የተገቡ አራቱ ጠባይዐት ናቸው፤ በዚያ ያለ እናት አባት አለው (መዝ ፪፥፯፤ ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም ያለምድራዊ አባት እናት አለችው (ሉቃ ፪፥፯) በዚያ ገብርኤል በፍርሀት ይቆማል (ሉቃ ፩፥፲፱) በዚኽም ገብርኤል በሐሤት የምሥራችን ይናገራል (ሉቃ ፩፥፳፮) በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው በዚኽም በቤተልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው (ሉቃ ፪፥፩-) በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል (ራእ ፰፥፫-) በዚኽም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ (ማቴ ፪፥፲፩) በዚያ ኪሩቤልና ሱራፌል ከግርማው የተነሣ ይንቀጠቀጣሉ በዚኽም ማርያም ዐቀፈችው ሰሎሜም አገለገለችው፤ በዚያ የመብረቅ ብልጭልጭታ በፊቱ ይገለባበጣሉ የእሳትም ወላፈን ከአዳራሹ ይወጣል (ሕዝ ፩፥፲፫) በዚኽም አህያና ላም በትንፋሻቸው አሟሟቁት (ኢሳ ፩፥፫) በዚያ የእሳት ዙፋን አለ በዚኽም የደንጊያ በረት አለ፤ በዚያ የእብነ በረድ የሰማይ ንጣፍ አለ በዚኽም የላሞች መጠጊያ በረት አለ፤ በዚያ የትጉሃን ሥፍራ በሰማያት ያለች ኢየሩሳሌም አለችው በዚኽም የእንስሳት ጠባቂዎች ማደሪያ በኣት አለው (ሉቃ ፪፥፯) በዚያ ርዝማኔ የማይታወቅ የዳንኤል ብሉየ መዋዕል አባት አለው (ዳን ፯፥፲፫-፲፬) በዚኽም የዓመቶቹ ቊጥር በሰው ልጅ ዐቅም መጠን የኾነ ሽማግሌ ዮሴፍ ተሸከመውየአምላክን ልጅ ሰው መኾኑን በዓል እናድርግ የተሸከመችውን ማሕፀን እናመስግን፤ ላቀፉት ጉልበቶች እንስገድ፤ ላሳደጉት ጡቶች እንዘምር፤ የዳሰሱትን እጆች እናመስግን፤ ለሳሙት ከንፈሮች እናሸብሽብ፤ ከእረኞች ጋር ምስጋናን እናቅርብ፤ ከሰብአ ሰገልም ጋር እጅ እንንሣ፤ እንደ ዮሴፍ እናድንቅ እንደ ሰሎሜም እናገልግል በተኛበት በረት እንስገድ፤ በተጠቀለለበት በረት እንበርከክ፤ ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና ይኹን በምድርም ሰውን ለወደደ እንበል (ሉቃ ፪፥፲፬) እግዚአብሔር ሰው ኾነ የሰው ልጅ ሴት ልጅም የእግዚአብሔር እናት ኾነች፤ ለርሱ ምስጋና ይኹን ለርሷም ስግደት ይገባል ለዘላለሙ አሜን ይኹን) በማለት በጥልቀት ገልጾታል፡፡

Comments